
የደምህት የታጠቀና የተደራጀ ኃይል ከኤርትራ መውጣት በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፀረ ሰላም ኃይሎች ህልውናን እንዲያከትም የሚያደርግ መሆኑ ሊቀመንበሩ አቶ ሞላ አስገዶም ገለፁ።
ኃይሉን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት አቶ ሞላ አስገዶም በሰጡት ይፋዊ መግለጫ ሁኔታው ለሻዕቢያ መንግስት ይሁን ለግንቦት ሰባትና መሰሎቹ ተስፋ አስቆራጭ ኪሳራ ነው ብለዋል።
የትግራይ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደምህት/ መስራች እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ሞላ አስገዶም በሀገሪቱ የነበሩ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች መፈታት አለባቸው የሚል አላማን በማንገብ የትጥቅ ትግልን አማራጭ በማድረግ ከ10 ዓመታት በላይ በኤርትራ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
የእርሳቸውንም ይሁን የሚመሩትን ከ800 በላይ የታጠቀ ሀይል አሁን በዋናነት 2 ጉዳዮች አካሄዱን እንዲያጤን አድርገውታል ብለዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ሁሌም ጥፋትን አንግቦ መንቀሳቀስ አንደኛው ሲሆን ነፍጥ እንዲያነሱ መነሻ የነበረው የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ምላሽ እያገኙ መምጣታቸው ደግሞ ሁለተኛው ነው፡፡
በዚህ መነሻም በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከአመት በላይ በጥልቀት መነጋገራቸውና መስራታቸው በሻዕቢያ አጋፋሪነት በኤርትራ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፀረ ሰላም ሃይሎች ብቸኛው የታጠቀና የተደራጀ ሀይል ያለው ደምህት ጠቅልሎ በስኬት ወደ ሀገሩ እንዲገባ አስችሏል ብለዋል፡፡
የግንቦት ሰባት አመራሮች ውጭ ካለው ዲያስፖራ ገንዘብ የማሰባሰቢያ ዓላማ ብቻ አንግበው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በተጨባጭ ማረጋገጣቸውንም ገልፀዋል።
አቶ ሞላ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ የግንቦት ሰባትና መሰሎቹን ህልውና እንዲያከትም የሚያደርግና ለሻዕቢያም ኪሳራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሪፖርተር:- አብዲ ከማል