የኤርትራ መንግስት ትንኮሳ የሚቀጥል ከሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ገልፀን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን – ጠ/ሚ ሀይለማርያም , July 07 2015

የኤርትራ መንግስት ትንኮሳ የሚቀጥል ከሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ገልፀን እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን - ጠ/ሚ ሀይለማርያም

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ እና ሌሎች አጎራባች ሀገሮችን ለማተራመስ የያዘውን አቋም የማይቀይር ከሆነ ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደምትወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ ከምክር ቤቱ “የኤርትራ መንግስት በቀጠናው እየፈፀመ ባለው የማተራመስ ድርጊት ለማስቆም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲፈጥር የማድረግ እና የኢትዮጵያ መንግስት አቋም ምን ይመስላል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ነው ይህንን ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስርት ኃይለማርያም በምላሻቸው “ከኤርትራ ጋር ያሉንን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ሙሉ ዝግጁነት አለን” ብለዋል።

“የኤርትራ መንግስት ግን ኢትዮጵያን እና ሌሎች አጎራባች ሀገራትን ለማተራመስ የያዘውን ስትራቴጂ የማይቀየር ከሆነ ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ገልፀን እርምጅ ለመውሰድ የምንገደድበት ሁኔታ ይፈጠራል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

“እርምጃውንም ለዓለም ህብረተሰብ አሳውቀን ነው የምንወስደው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ፥ እስከዚያ ድረስ ግን የኤርትራ መንግስት ለእየአንዳንዷ ለሚያከናውናት ትንኮሳ የተመጣጠነና ዓለም ዓቀፍ ህግን የተከተለ እርምጃ ስንወስድ መጥተናል  አሁንም ይህንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል” ብለዋል።

ወንድም የሆነው የኤርትራ  ህዝብ ሲሰቃይ እንዲሁ መመልከቱ  ተገቢ ባለመሆኑም ኢትዮጵያ ያለባትን ሀላፊነት ትወጣለች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር በተያያዘ “ዘንድሮ ለባለ እድለኞች የተላለፉት ዋጋቸው መወደዱ  ይነሳል” በሚል ለተነሳው ጥያቄ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ የቤት መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት ከ1996 ጀምሮ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል።

የዘንድሮውም ቢሆን ከዚህ በፊት ሲተላለፉ እንደነበሩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች መጨመሩን በማንሳት የዘንድሮው ግን የተለየ ጭማሪ እንዳልተደረገበት ነው የተናገሩት።

አንዳንድ ሰዎች በቤት ምዝገባ  ወቅት አቅማቸው የሚፈቅደውን  መርሃ ግብር መርጦ በመመዝገቡ ላይ  ችግሮች እንደነበሩ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም፥ በተለይም ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ የህብረተሰብ ክፍሎች በ10/90 መርሃ  ግብር ላይ መመዝገብ ሲገባቸው በ20/80 መርሃ  ግብር ላይ ተመዝግበዋል።

ይህም በመሆኑ ለ10/90 መርሃ ግብር የተገነቡ ቤቶች ከተመዝጋቢው ቁጥር መብለጣቸውን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ ግን በተለይም ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ ለተጠቃሚ የተላለፉ ቤቶች 50 በመቶ ወጪያቸው በመንግስት መደጎሙን ተናግረዋል፤ 16 ቢሊየን ብር ከነበረው የቤቶቹ ግንባታ ወጪ ውስጥ መንግስት 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪው በመንግስት መደጎሙን በመግለፅ።

በመዲናዋ የሚስተዋለውን ትራንስፖርት እጥረት በተመለከተ

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት እጥረትን ለመፍታትም የቅንጅት ስራዎች እና የቁጥጥር ስራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

የእነዚህ ተግባራት በበቂ ሁኔታ  አለመፈታትም ችግሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረጉንም ነው ያነሱት።

በመሆኑም የመደበኛ አውቶብስ አገልግሎት፣ የታክሲ፣ የድጋፍ ሰጪ እና የሌሎችም  የትራንስፖርት አግልግሎቶች በቅንጅት እንዲመራ ከማድረግ በተጨማሪ፥ የግል ባለሃብት በዘርፉ እንዲሳተፍ በማድረግ ረገድም 500 አውቶብሶች ከቀረጥ ነፃ ገብተው ስራ እንዲጀምሩ የማመቻቸት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በተጨማሪም መንግስት እና ባለሃብቶች በትራንስፖርቱ ዘርፍ ተቀናጅተው መስራት በሚጀምሩበት ወቅትም የመዲናዋን የትራንስፖርት እጥረት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚቻል ነው የገለፁት።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት በታሰበው ጊዜ ስራ እንዳይጀምር ያደረገው የ450 ኪሎ ሜትር የገመድ ዝርጋታን ለማከናወን የግዢ ሂደቱ በፍጥነት ባለመከናወኑ መሆኑን ጠቁመው አሁን የግዢ ሂደቱ አሁን እልባት በማግኘቱ በቅርቡ ወደስራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ

በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ መንግስት ሰፊ ስራዎችን ያከናወነ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያውያኑ ተሳትፎም የማይናቅ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ይሁንና በሚፈለገው ደረጃ  ላይ ደርሷል ብሎ ለመናገር ግን ብዙ የሚቀሩ ነገሮች በመኖራቸው፥ በቀጣይ መንግስት በትኩረት እና በመቀራረብ የሚሰራበት ጉዳይ ይሆናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በተጠናቀቀው እና በቀጣዩ የአገሪቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዙሪያ በማወያያትም ጠቃሚ ግብዓቶችን ለማግኘት መንግስት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ መንግስት እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት እንዳሉ ሆኖ ወላጆች፣ የእምነት አባቶች እና በአጠቃላይ የማህበረሰቡ የቅንጅት ስራዎች ወሳኝነት ሊሰመርበት እንደሚገባ  አንስተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ከአለም አቀፉ የፖሊስ ሀይል/ኢንተርፖል ሃላፊ ጋር በመመካከር በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳታፊ የሆኑ ደላሎችን መረብ በጋራ  ለመበጣጠስ የቅንጅት ስራዎች በሚከናወኑበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት መደረሱን ነው የጠቀሱት።

የምርምር ስራዎችን ማጎልበት

አቶ ሀይለማርያም ምርምርን በተመለከተ በአገራችን ያለው ተሞክሮ አንስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማየት የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው፥ በተወሰነ ደረጃ የግብርና ምርምር ስራዎች ላይ የታዩ አበረታች ጅምሮች ግን የሚናቁ አይደሉም ብለዋል።

ለዚህም የሰለጠነ የሰው ሃይል እና የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት የሚጠቀሱ ቢሆንም በቀጣይ ግን መንግስት ሰፊ እና ጥልቅ እንዲሁም ችግር ፈቺ ለሆኑ ምርምሮች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ለአብነትም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምርን ለመተግበር በአመት 100 ሚሊየን ብር ተመድቦ እየተሰራበት እንደሚገኝ አንስተዋል።

 

የተጫነው፡- በሙለታ መንገሻ

– See more at: http://www.fanabc.com/index.php/news/item/8816-%E1%8B%A8%E1%8A%A4%E1%88%AD%E1%89%B5%E1%88%AB-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%89%B5%E1%8A%95%E1%8A%AE%E1%88%B3-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%89%80%E1%8C%A5%E1%88%8D-%E1%8A%A8%E1%88%86%E1%8A%90-%E1%88%88%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A5-%E1%8C%88%E1%88%8D%E1%8D%80%E1%8A%95-%E1%8A%A5%E1%88%AD%E1%88%9D%E1%8C%85-%E1%88%88%E1%88%98%E1%8B%8D%E1%88%B0%E1%8B%B5-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%88%E1%8B%B0%E1%8B%B3%E1%88%88%E1%8A%95-%E1%8C%A0-%E1%88%9A-%E1%88%80%E1%8B%AD%E1%88%88%E1%88%9B%E1%88%AD%E1%8B%AB%E1%88%9D.html#sthash.LjuWQmIi.dpuf

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *